ከአማራ ማህበር በአሜሪካ የተሰጠ መግለጫ
ታኅሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ዲሴምበር 13, 2024
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ ላይ የሚደረገውን የዘር ማጥፋት ለማስቆም እርምጃ ሊወስድ ይገባል
በአብይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ ባለስልጣናት እና ታጣቂ ኃይሎች እያደረሱ ያሉት በአማራ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠሩ የሰብዓዊ መብት ረገጣውች፣ ስደት እና የጥቃት ቅስቀሳዎች እንዳሳሰቡት የአማራ ማህበር በአሜሪካ ስጋቱን ይገልጣል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጨመረው ቅስቀሳ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል እየደረሰ ያለው በደል ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን የኦሮሞ ብልፅግና አገዛዝ በአማራ ክልል እየፈጸመ ያለው እስከ ጦር ወንጀልና በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀም ወንጀል የሚደርስ የዘር ማጥፋት ጦርነት ቀጥሏል።
ከጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል፣ የኦሮሞ ሚሊሻዎች እና አጋር ኃይሎች በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ሰሜን ሸዋ እና የአካባቢው ዞኖች በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰት ፈፅመዋል። ይህ ዘመቻ «ትጥቅ ማስፈታት» በሚል ሽፋን በህጋዊ መንገድ የተመዘገበ መሳሪያ በገጠሩ ከሚኖሩ አማራዎች እንዲወረስ የታወጀ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ከፍርድ ውጪ የሚፈፀሙ ግድያዎች፣ ጾታዊ እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ማሰቃየት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ ፣ የግዳጅ ውትድርና፣ አስገድዶ ማፈናቀል፣ የንብረት ውድመት እና የዘረፋ ዘመቻዎች ተያይዘው መካሄዳቸውን ያሳያሉ። እነዚህ ጥቃቶች ማንንም ያለዩ አማራ ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ህጻናትን እና አረጋውያንን ሰለባ ያደረጉ ሲሆኑ ባለፈው ሳምንት ብቻ የተጎጂዎቹ ቁጥር በመቶዎች ምናልባትም በሺዎች የሚቆጠር እንደሚሆን ይገመታል። እነዚህ ማህበረሰቦች ከዚህ ቀደም ከጸጥታ ኃይሎች ምንም ዓይነት ጥበቃ ባለማግኘታቸው በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ከፍተኛ የሆነ የዘር ማጥፋት እልቂት እንደደረሰባቸው (እየደረሰባቸውም እንደሆነ) ይታወቃል።
የፌደራል እና የክልል ባለስልጣናት የፀጥታ ተቋማቱ ለእነዚህ ዜጎች አስተማማኝ ጥበቃ የመስጠት አቅም እንደሌላቸው በመግለፃቸው ሰዎቹ በራሳቸው ወጪ ራሳቸውን የሚከላከሉበት መሳሪያ ገዝተው ታጠቁ ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሚያስደነግጥ ሁኔታ የጸጥታ ኃይሎቹ ከኦነግ ታጣቂዎች ጋር በመተባበር እነዚህን ማህበረሰቦች እየመረጡ በግዳጅ ትጥቅ በማስፈታት እና የተወረሱ መሳሪያዎችን ለታጣቂዎች በማከፋፈል ማህበረሰቦቹ ከለላ እንዳይኖራቸው በማድረግ ለዘር ማጥፋት እልቂት ተጋላጭ እንዲሆኑ እያደረጉ ይገኛሉ።
በኦሮሚያ ክልል በአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት በመንግስታዊ መዋቅር የተደገፈ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ያደረገ የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማፅዳት እና ሙሉ መንደሮችን ማጥፋትን ያካተተ ዘርፈ ብዙ የተመዘገበ ታሪክ ያለው ነው። የአማራ ማህበር በአሜሪካ በኦሮምያ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመንግስት ባለስልጣናት የተሳተፉበት የዘር ማጥፋት እልቂቶችን የመዘገበ ሲሆን በእነዚህም እልቂቶች በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ሴቶች፣ ህፃናት፣አዛውንቶች እና አካል ጉዳተኞች ሲገደሉ ከ2 ሚሊዮን በላይ የዘር ማፅዳት ተፈፅሞባቸዋል። ይህ ሆነ ተብሎ እየተደረገ ያለ ወንጀል አብይ አህመድ እና የኦሮሞ ብልፅግና አገዛዙ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ላለፉት 6 ዓመታት ቀጥሏል። በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ ከዘር ጭፍጨፋው አምልጠው በሕይወት የተረፉ ሰዎች በአጎራባች አማራ ክልል በሚገኙ የስደተኛ መጠለያዎች የጸጥታ ችግር፣ ጾታዊ እና ጾታ ተኮር ጥቃት ተጋርጦባቸው በምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ የጤና እና ሌሎችም መሠረታዊ አቅርቦቶች ተከልክለው ይገኛሉ።
ይህ እየተካሄደ ያለው ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ 20ኛ ወር የሆነውን የኦሮሞ ብልፅግና አገዛዝ በአማራ ክልል እያደረገ ያለውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ እና ከበባ እየተባባሰ መምጣቱን የሚያመላክት ነው። የኦህዴድ አገዛዝ ወታደራዊ ሽንፈቶች እና እክሎች እያጋጠሙት በመሆኑ፣ ብጥብጥን ማነሳሳት፣ የጥላቻ ንግግሮችን እና የግዳጅ ውትድርናን በመጠቀም ስልጣኑን በህገወጥ መንገድ ለማራዘም እየሞከረ ይገኛል። ኅዳር 2017 ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በነቀምቴ ለህዝብ ባደረጉት በክልሉ በሚኖሩ የአማራ ማህበረሰቦች ላይ ጥቃትን የሚቀሰቅስ ንግግራቸው የፓርቲያቸው ራዕይ የሆነውን «አማራን ከምድረ ገፅ የማጥፋት» አላማ እንደሚያስፈፅሙ ቃል ገብተዋል።
በእርግጥም በአማራው ላይ እየተካሄደ ባለው ከበባ የኦሮሞ ብልፅግና አገዛዝ ተመሳሳይ ንግግሮችን በመጠቀም ድጋፍ ለማግኘት፣ በግዳጅ የሚደረግ የወታደራዊ ምልመላ ቁጥርን ለመጨመር በመጠቀም የጅምላ ጭፍጨፋዎችንና የጦር ወንጀሎችን በማቀጣጠል ላይ ይገኛል። አገዛዙ በኦሮሚያ በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ አነጣጥሮ በግዳጅ ትጥቅን በማስፈታት በመላ ሀገሪቱ ለማካሄድ ላቀደው የዘር ማጥፋትና የአማራን ዘር የማፅዳት ዘመቻ መሠረት በመጣል ላይ ነው።
የአማራ ማህበር በአሜሪካ እየተባባሱ የመጡት ጥቃት ቀስቃሽ ንግግሮች እና ተያይዞ የጨመረውን የጅምላ ጭፍጨፋ ስጋቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለጥቃቱ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን ለመጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪውን ያቀርባል። በተለይም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች የኦህዴድ አገዛዝ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን በደል እንዲያወግዙ እና አገዛዙ በዚሁ ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን ጥሪውን ያቀርባል። የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የዓለም የገንዘብ ድርጅትን እና የዓለም ባንክን ጨምሮ ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እየፈፀመ ለሚገኘው የኦሮሞ ብልፅግና አገዛዝ የሚያደርጉትን ማንኛውንም የገንዘብ ድጋፍ ወይም እርዳታ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ማህበሩ ጥሪውን ያቀርባል። ዓለም በአንድ ወቅት የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ተከትሎ «በፍፁም የማይደገም» ብሎ የነበረ ቢሆንም ዛሬም በአማራ ህዝብ ላይ የሚደረገውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመከላከል እርምጃ መውሰድ ተስኖታል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህንን ለማስቆም በፍጥነት ጣልቃ መግባት አለበት። ዝምታ ከወንጀል ጋር መተባበር ነው።
Comments