top of page
  • Writer's pictureAAA-admin

ከአማራ ማህበር በአሜሪካ የተሰጠ መግለጫ



በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አማራ ንፁሃን እየተገደሉ ዓለም አቀፍ ኃይላን እንዳላዩ ፊታቸውን አዙረዋል አንዳንዶቹም የአብይ አህመድን የዘር ማጥፋት ዘመቻ በመደገፍ ላይ ይገኛሉ 


መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም. (ሴፕቴምበር 17, 2024) 


የአማራ ማህበር በአሜሪካ ባወጣው አዲስ ዓመታዊ የጉዳት መረጃ እንደሚያሳየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ኅምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል እና የአማራ ተወላጆች በሚኖሩባቸው በሌሎችም አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ አማራ ንፁሃን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል። ምንም እንኳን መረጃው የጉዳቱን መጠን በከፊል ብቻ የሚያሣይ ቢሆንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ወዲህ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱን በጉልህ ያሳያል። ይህ የጭካኔ እርምጃ ከሚያዝያ 2015 ጀምሮ ለወራት የተካሄደውን ፀረ-መንግስት ሰላማዊ ተቃውሞዎችን ተከትሎ የቀጠለ ነው። በመረጃው የተመዘገቡት የሰላማዊ ሰዎች ጭፍጨፋዎች፣ ያለ ፍርድ የሚደረጉ የዘፈቀደ ግድያዎች እንዲሁም ሌሎች ግፎች የጦር ወንጀል እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ተብሎ ሊቆጠር የሚችል ሲሆን እንዲሁም ለአስርት ዓመታት ሲቀጥል የመጣው በኢትዮጵያ በአማራ ላይ የሚደረገው የዘር ማጥፋት አንዱ ክፍል ነው።


ከኅምሌ 28 ቀን 2015 እስከ ኅምሌ 28 ቀን 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት፣ በትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) እና በሌሎችም ተባባሪ ኃይሎች የተፈጸሙትን የዘር ማጥፋት ድርጊቶች የአማራ ማህበር በአሜሪካ እንደሚከተለው መዝግቧል:


  • በአማራ ክልል፣ በአዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎች የአማራ ተወላጆች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በ16 ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ከ200 በላይ ጭፍጨፋዎች (ሰው አልባ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጨምሮ) ተፈፅመው ባጠቃላይ በ3,283 ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን 2,592 ንፁሀን ዜጎች ሲገደሉ 691 ቆስለዋል፤


  • በሰላማዊ ዜጎች ላይ እና በመሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ ቢያንስ 53 የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃቶች የተፈፀሙ ሲሆን በዚህም 551 ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሶ 433 ሲሞቱ 118 ቆስለዋል፤


  • 269 ሰዎች ላይ አስገድዶ መድፈር የተፈፀመ ሲሆን የዚህ ወንጀል ሰለባዎች አብዛኛዎቹ ወጣት ልጃገረዶችና ሴቶች ሲሆኑ በጥቂቱ ወንድ ቄሶች እና ወጣት ወንዶችም ሰለባ ሆነዋል፤


  • በትምህርትና በጤና ተቋማት ላይ እየደረሰ ባለው ጥቃት ከ4.1 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በትምህርት ገበታቸው ላይ በመገኘት ያልቻሉ ሲሆን በክልሉ 4,178 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤


  • በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የዘፈቀደ የማስቆም እና መፈተሽ ተግባር፣ አስገድዶ ገንዘብ መቀበል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች የጅምላ እስር፣ የእስረኞች አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥቃት፣ ቤተሰብ እንዳይጎበኝ መከልከል፣ የበቂ ህክምና አገልግሎት መነፈግ እና የንጽህና እጦት፤


  • በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የአማራ ተወላጆች ፋኖን ይደግፋሉ ወይም ለፋኖ ይሰልላሉ በሚል ክስ ከስራ መባረር፤


  • በአማራ ክልል እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይዘገቡ የቴሌኮሙኒኬሽን እና የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጥ፤


  • በኦሮሚያ ክልል በአማራው ላይ ከሚደረገው የዘር ማጥፋት የተረፉትን አማራዎች በግዳጅ ከአማራ ክልል ወጥተው እንዲፈናቀሉ ማድረግ፤


  • እንደ አካባቢው የሰብዓዊ ዕርዳታ ባለሥልጣናት ግምት በደርዘን የሚቆጠሩ ምናልባትም በመቶዎች የሚቆጠሩ በረሃብ እየሞቱ ባሉብት የአማራ ክልል ሕይወት አድን ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሕይወት አድን ዕርዳታ መዘጋት፤


የምርመራው አጽነኦት እንደሰጠው የቴሌኮሙዩኒኬሽን መቆራረጥ እና በቦታው ያለው የጸጥታ ችግር ምርመራውን በጥልቀት ለማካሄድ አስቸጋሪ ስላደረጉት የተዘረዘሩት አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች እና ጥቃቶች የትክክለኛውን የጥቃት መጠን አነስተኛ ክፍል ብቻ እንደሚያሳዩ ተገልጿል። በምርመራው ላይ እነዚህ ውሱንነቶች ቢኖሩም ግኝቶቹ በተከታታይ እየተፈጸሙ ያሉ የጦር ወንጀሎችን፣ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን እና ለአስርት አመታት የዘለቀው የአማራ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ከኦሮሚያ ክልል ወደ አማራ ክልል እየሰፋ መሄዱን ያሳያል።


የሚካሄደውን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ቢኖሩም ምዕራባውያን መንግስታት የአብይ አህመድ መንግስት እየፈጸመ ያለውን ግፍና በደል ለማውገዝ አሁንም ፈቃደኞች አይደሉም። ይልቁንም በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ በብድር እና በቀጥታ የበጀት ዕርዳታ የገንዘብና ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። በትግራይ ውስጥ ውጊያ በሚካሄድበት ወቅት ያደርጉ ከነበረው ጠንካራ ግፊት በተቃራኒ በአማራ ክልል ለተፈጠረው ችግር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዝምታን መርጧል። እንደ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ፣ ቱርክ፣ ቻይና እና ኢራን ያሉ ሀገራት በቀጥታ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚሰማሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና የጦር መሳሪያዎችን ለአገዛዙ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል። የአውሮፓ ሀገራት እና አሜሪካ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የአለም ባንክ አገሪቷን በድህነት አረንቋ ውስጥ የሚከት የኢኪኖሚ ፖሊሲ ለውጦች እንዲተገበሩ በማስገደድ አቢይ በአማራ ላይ ለሚያካሂደው ጦርነት በብዙ ቢሊዮን ዶላር ብድር እንዲሰጥ ፈቅደዋል።


የአብይ አህመድ መንግስት የሚያደርጋቸው ድርጊቶች ለኢትዮጵያ እና ለአካባቢው ሃገራት መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል። በአማራ ክልል እና በሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል ለማስቆም እና ተጨማሪ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ለማድረግ በአብይ አህመድ ላይ ግፊት ማድረግ የሚችሉ አካላት ሁሉ ቆራጥ እርምጃ እንዲወስዱ የአማራ ህዝብ ያሳስባል። ነገር ግን የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ውጤታማ እርምጃ አለመውሰዱን በማጤን የአማራ ህዝብ የወደፊት ዕድሉን ራሱ ለመወሰን በቁርጠኝነት ተነስቷል። በውጫዊ ድጋፍም ሆነ ያለ ድጋፍ ህልውናውን እና መብቱን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ጸንቷል።





Comentários


bottom of page