
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አብይ አህመድ በአማራው ላይ የሚፈፅመውን የዘር ማጥፋት ጦርነት እንዲቀጥል ማስቻሉንና እና የፕሪቶሪያ ስምምነት ጦርነት አስቁሟል የሚለውን የሐሰት ንግግር ማቆም ይኖርበታል
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በአብይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ በኢትዮጵያ በአማራ ሕዝብ ላይ እያካሄደ ያለውን የዘር ማጥፋት ጦርነትን ለማስቆም ዓለም አቀፍ መሪዎች እያሳዩት ያሉት ቸልተኝነት በጽኑ ያወግዛል። መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች አጋር መንግስታት ኤምባሲዎች በቅርቡ ባወጡት መግለጫ የጥቅምት 2015 ዓ.ም. ስምምነት ጠመንጃውን ዝም እንዳሰኘ አድርጎ ገልጿል። ይህ አገላለጽ አሳሳች ብቻ ሳይሆን ሆን ተብሎ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን የአማራን የዘር ማጥፋት ጭካኔ የተሞላበት እውነታ ወደ ጎን መተው ነው።
የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ ጠብመንጃውን ዝም ከማሰኘት በራቀ ሁኔታ በአማራ ንፁሀን ዜጎች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ በመክፈት ከቤት ለቤት እልቂት፣ ሆን ብሎ የክልሉን የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት እስከ ማውደምና የሰው አልባ አውሮፕላኖች ድብደባ በማካሄድ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠላማዊ ዜጎችን ገድሏል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የፕሪቶርያ ስምምነት ጠብመንጃውን ጸጥ አሰኝቷል በማለት የዓለም ዲፕሎማቶች ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ወደ መደበኛ ግንኙነት እያስተካከሉ ይገኛሉ። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በእነዚህ አረመኔያዊ ድርጊቶች ላይ ያሳየው ዝምታ አሳፋሪ እና ለድርጊቱ አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።
የአማራ ማኅበር በአሜሪካ የፕሪቶርያ ስምምነት አግላይ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ የተሳተፉትን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያላካተተ እንደሆነ በተደጋጋሚ አስጠንቅቋል። በሰሜኑ ጦርነትም ሆነ ከበርካታ አስርት አመታት በፊት በኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ እና በትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) የዘር ማጥፋት ጥቃት እየደረሰበት የሚገኘው የአማራ ህዝብ ሆን ተብሎ ከድርድሩ እንዲገለል ተደርጓል። የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአማራን ሕዝብ ከስምምነቱ መገለል ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ በአማራ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያለ ተጠያቂነት ጦርነት እንዲከፍት አስተዋጽኦ አድርጓል። ኢትዮጵያውያን እና የአካባቢው ተንታኞች ስምምነቱ የታሰበውን ውጤት እንደማያመጣ ቀደም ብለው ያመኑ ቢሆንም በሚያሳዝን ሁኔታ የዓለም ዲፕሎማሲያዊ ማህበረሰብ ይህንን እውነታ ለመቀበል አሁንም አሻፈረኝ እንዳሉ ይገኛሉ።
ከዝምታው ባሻገር የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ የጀመረውን አማራን የማጥፋት ጦርነት ሲያካሂድ የዓለም ማኅበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። ምንም እንኳን እየተፈጸሙ ያሉ የጦር ወንጀሎች እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እጅግ ብዙ ቢሆኑም ኀምሌ 2016 ዓ.ም. የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የ20 ቢሊየን ዶላር ፓኬጅ አፅድቀዋል። ይህ የገንዘብ ድጋፍ አገዛዙ በአማራ ህዝብ ላይ የጀመረውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለማስቀጠል ያለውን አቅም ለማጠናከር አገልግሏል። በተጨማሪም በአማራ ህዝብ ላይ የሚካሄደው ጦርነት እየተፈፀመ እያለ የካናዳ መንግስት ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ያለውን ወታደራዊ ትብብር ለማደስ በቅርቡ ያሳለፈው ውሳኔ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ቅንነት የጎደላቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው። የዘር ማጥፋትን እና የጅምላ ግድያዎችን በተደጋጋሚ ከሚፈጽም ሰራዊት ጋር የሚደረግ ወታደራዊ ተሳትፎ ካናዳን በቀጥታ ከእነዚህ ወንጀሎች ጋር ያነካካታል።
በትግራይ ውስጥ የተከሰተው የውስጥ ችግር አሳሳቢ ቢሆንም ነገር ግን በኦሮሞ ብልጽግና እና በኤርትራ መካከል ይፈጠራል የሚባለው የጦርነት ስጋት የተጋነነ ነው። ላለፉት ሁለት ዓመታት የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ ሙሉ ወታደራዊ ኃይሉን ከአማራ ፋኖ መከላከያ ሠራዊት ጋር ለሚያደርገው ሁለንተናዊ ጦርነት በአማራ ክልል አሰማርቷል። ስለሆነም የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ ከውጪ አገራት ጋር ሌላ ጦርነት ለማካሄድ የሚያስችል ወታደራዊ የሰው ኃይል እና የግዛት መሠረት እንደሌለው ግልፅ ነው። እየተካሄዱ ያለት ከኤርትራ ጋር “የማይቀር” ጦርነት የሚሉ የማስጠንቀቂያ ንግግሮች የዓለም አቀፍ ተዋንያን በዝምታ እያለፉት ያለውን በአማራ ሕዝብ ላይ የተከፈተውን የዘር ማጥፋት ጦርነት የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር የሚደረግ ሙከራ ነው።
ጦርነትን ለመከላከል እና በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ሠላምን ለማምጣት ተጠያቂነትን ማስፈን እና የሽግግር ፍትህን ማምጣት ብቸኛና ትክክለኛ መንገዶች ናቸው። ዓለም አቀፍ ተዋናዮች እውነተኛ ሠላም የሚፈልጉ ከሆነ የፕሪቶርያ ስምምነትን ጉድለቶች አምነው ከስህተቱ በመማር የብልጽግና አገዛዝ በአማራ ላይ የሚያደርሰውን የዘር ማጥፋት ጦርነት በማውገዝ የአብይ መንግስት ጥቃቱን እንዲያቆም እና ተዓማኒነት ያለው የዘር ማጥፋት እና የጦር ወንጀል ምርመራ እንዲደረግ እስኪፈቅድ ማንኛውንም የገንዘብ እና ወታደራዊ እርዳታ ማቆም ይኖርባቸዋል። እንዲሁም በአገዛዙ እና በደጋፊዎቹ ላይ ማዕቀብ በመጣልና የተለያዩ ሕጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ተጠያቂነትን ማስከበር አለባቸው። ርምጃ አለመውሰድ ዘላቂ የሞራል እድፍ የሚፈጥር ሲሆን ለዓለም አቀፍ ጥቅም አስጊ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። የአማራ ማኅበር በአሜሪካ ፣ ዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች እና አጋሮች በአማራ ላይ ለሚደረገው የዘር ማጥፋት ወንጀል ፍትህ እንዲሰፍን እና ተጠያቂነት እንዲመጣ በቀጣይነት ያሳስባል።
Comments