የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ትሕነግ እና የብልፅግና ፓርቲ አገዛዝ የራያ አማራዎች ላይ እያደረሱ ያሉትን ጥቃት ሊያወግዝ ይገባል
የአማራ ማህበር እንደተረዳው ዛሬ ሚያዝያ 7/2016 ዓ.ም. የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) በራያ አላማጣ አማራዎች ላይ የሚያደርገውን ጥቃት በማስፋፋት የሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ፣ የሰብዓዊ ቀውስ እንዲፈጠር እና የጦርነት የስጋት በአካባቢው ላይ እንዲያንዣብብ አድርጓል።
ተዓማኒ የሆኑ ምንጮች እንደገለፁት የአላማጣ ከተማ ሚካናይዝድ በሆነ የትሕነግ ሠራዊት ኃይል የተከበበ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከከተማው ተፈቀናቅለው በደቡብ አቅጣጫ ወደሚገኘው ራያ ቆቦ ተሰደዋል። የአማራ ማህበር በአሜሪካ ለዓመታት እንዳስጠነቀቀው ይህ ትሕነግ የፈፀመው ጥቃትና የጦርነት እንቅስቃሴ አደጋ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በሚመራው የኦሮሞ ብልጽና ፓርቲ አገዛዝ ድጋፍና ትዕዛዝ የሚፈፀም ነው። እንዲሁም ይህ የትሕነግ ወራሪ ኃይል በአማራ ክልል አስተዳደር ሥር ይተዳድሩ የነበሩትን እነዚህን አካባቢዎች ለመረከብ የትግራይ አስተዳደር አዋቅሯል። ይህ ወረራ የተፈፀመው በጌታቸው ረዳ በሚመራውና የትሕነግ ወኪል በሆነው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በአቶ አረጋ ከበደ የሚመራው የአማራ የብልጽና ፓርቲ አገዛዝ የተካተተበት የብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ ከፈፀሙት ሚስጥራዊ ስምምነት በኋላ ነው። ይህ በድብቅ የተካሄደው ስምምነት ለረዥም ጊዜያት የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ የሆኑትን እና በአፓርታይድ መሰል የትግራይ አገዛዝ ሥር ለመኖር ተገደው የነበሩትን የራያ አማራዎች ፍላጎትና መሠረታዊ መብቶች አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ይህ ጉዳይ የሚያሳዝን ቢሆንም የተለያዩ ባለሙያዎች ኅዳር 2015 ዓ.ም. የተፈረመው የሠላም ስምምነት ጉዳዩ የሚመልከታቸውን አካላት ያገለለ በመሆኑ ሌላ “የጦርነት ስምምነት” እንደሆነ በመግለፅ ሲያስጠነቅቁ የነበረ በመሆኑ ያልተጠበቀ ጉዳይ አልነበረም። የራያ ነዋሪዎች የአማራ ማህበር በአሜሪካ፣ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና የብዙሃን መገናኛዎች እንደሰነዱት በሠሜኑ ጦርነት ወቅት ለተጨፈጨፉባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን እና ለወደሙ ንብረቶቻቸው ፍትህን ሲጠይቁ ይህ መፈፀሙ ልብን የሚሰብር ነው። ይህ የትሕነግ ወረራ አገሪቱን የበለጠ ወደ አለመረጋጋት የሚገፋ እና በአማራ ክልል የተፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ የሚያባብስ እንደሆነ የአማራ ማህበር በአሜሪካ ያምናል።
በመሆኑም ዓለማቀፍ መሪዎች፣ የመብት ድርጅቶች እና ተፀዕኖ ማድረግ የሚችሉ አካላት የብልጽና ፓርቲ አገዛዝ እና ትሕነግ ራያ አካባቢንም ሆነ በሊሎች የአገሪቷ ክፍሎች የሚገኙ የወሰን ጥያቄ ያለባቸውን ቦታዎች ኃይልን በመጠቀም ከመውሰድ እንዲቆጠቡ ግፊት እንዲያደርጉ የአማራ ማህበር በአሜሪካ ይጠይቃል።
Comments