የዐማራ ማህበር በአሜሪካ (Amhara Association of America) ከፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ማእከል (Centre for Human Rights, Pretoria University) ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል በዐማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን በመንግስት መዋቅር የሚደገፍ መጠነሰፊ ዘር ተኮር ጭፍጨፋና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ የኢትዮጲያ መንግስትን በመክሰስ ለአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን (African Commission on Human and Peoples' Rights) አቤቱታ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተ ለዐማራ ህዝብ እንዲሁም ጉዳዩ ይመለከተናል ብለው ለሚያስቡ አካላት ሙሉ ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ አጠር ያለ ማብራሪያ መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም ቅሬታው ስለቀረበለት የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን (ከዚህ በኋላ አፍሪካ ኮሚሽን በሚል የሚጠቀስ) ምንነትና አሰራር፣ ስለ ቅሬታው ይዘት፣ የቅሬታው ፋይዳ እንዲሁም ወደፊት መደረግ ስላለባቸው እንቅስቃሴዎች በተመለከተ የሚከተለው ማብራሪያ ቀርቧል፡፡
የአፍሪካ ኮሚሽን ምንነትናቅሬታዎችን ተቀብሎ የመመርመር ስልጣን
የአፍሪካ ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ1981 ናይሮቢ፣ ኬንያ ላይ በተካሄደው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ 2002 ጀምሮ አፍሪካ ህብረት ተብሎ በአዲስ መልክ የተቋቋመ) አሥራ ስምንተኛው የመሪዎች ጠቅላላ ጉባኤ ይሁኝታ አግኝቶ በአፍሪካ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችንና መሠረታዊ ነፃነቶችን ለማራመድና ለመጠበቅ የወጣውን የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተርን (በተለምዶ የባንጁል ቻርተር ተብሎ የሚገለጽ) አተገባበር በተመለከተ የበላይ ጠባቂነትና ተርጓሚነት ሥራን እንዲሰራ የተቋቋመ በከፊል የፍ/ቤት ባህሪ ያለው አህጉራዊ ተቋም ነው፡፡ የኮሚሽኑ መቀመጫ በጋምቢያ ዋና ከተማ ባንጁል ሲሆን በየ ስድስት አመቱ ባላቸው ስነምግባርና መልካም ስም ፣ በሰብአዊ መብቶች መስክ ባላቸው ችሎታና የህግ ልምድ የባንጁል ቻርተርን ከተቀበሉ የአፍሪካ አገሮች በሚመረጡ 11 ባለሙያዎች የተዋቀረ ተቋም ነው፡፡ የባንጁል ቻርተርን የተቀበሉ አባል ሀገሮች (ኢትዮጲያን ጨምሮ) በቻርተሩ ተቀባይነት ያገኙትን መብቶችና ነጻነቶችን በአግባቡ ይተገበሩ ዘንድ የአፍሪካ ኮሚሽን የመቆጣጠርና የመከታተል ስልጣን ያለው ሲሆን ይህም ስለ መብቶቹና ነጻነቶቹ ግንዛቤ የማስፋፋት፣ የማስጠበቅና የማስከበር ሀላፊነቶችን ይጨምራል፡፡ በቻርተሩ ላይ እውቅና የተሰጣቸውን መብቶችና ነጻነቶች የማስጠበቅና የማስከበር ሀላፊነቱን ለመወጣት ለ ኮሚሽኑ ከተሰጡት ስልጣኖች መካከል በአባል ሀገራት ላይ የሰብአዊ መብቶችን በተመለከተ በግለሰቦች ወይም መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን (individual complaints) የመቀበል፣ የመመርመርና የውሳኔ ሀሳብ የመስጠት ስልጣኑ ይገኝበታል፡፡ ይህንን የቅሬታ አቀራረብ ስርአት በመጠቀም በባንጁል ቻርተር እውቅና የተሰጣቸው መብቶች ጥሰት ሰለባ የሆኑ ግለሰቦችና ድርጅቶች ወይም እነሱን በመወከል ለሰብአዊ መብቶች መከበር የቆሙ ግለሰቦችና ድርጅቶች በአባል ሀገራት ላይ ክስ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ የዐማራ ማህበር በአሜሪካም ይህንን የቅሬታ አቀራረብ ስርአት መሰረት በማድረግ ከፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ማእከል ጋር በጋራ በመሆን የኢትዮጲያ መንግስት በኦሮሚያ ክልል በዐማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን መጠነሰፊ ዘር ተኮር ጭፍጨፋና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ባለማስቆሙና በባንጁል ቻርተር እውቅና ያገኙ መብቶች ና ነጻነቶችን የማክበርና የማስከበር ግዴታውን ባለመወጣቱ ተጠያቂነት አለበት ሲል ለኮሚሽኑ ቅሬታውን አስገብቷል፡፡
የ ቅሬታው ይዘት
የዐማራ ማህበር በአሜሪካ ከፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ማእከል ጋር በመተባበር ያቀረበው ቅሬታ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሮ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ምእራብ ሸዋ ዞኖች በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ሀይሎች አማካኝነት ባለፉት ሁለት አመታት ( እ.ኤ.አ 2021 እና 2022) ለጅምላ ጭፍጨፋና መጠነሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እየተጋለጡ ያሉ የዐማራ ብሄር ተወላጆችን የሚመለከት ሲሆን በቀረበው ቅሬታ ላይ የሚከተሉት ነጥቦች ተነስተዋል፡፡
የዐማራ ህዝብ እ.ኤ.አ ከ1991 ጀምሮ ዐማራነትን በጠላትነት ፈርጀው በተነሱት በትህነግ (በትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር) እና በኦነግ (በኦሮሞ ነጻነት ግንባር) አማካኝነት በተጫነበት ዐማራ ጠል የጎሳ ፌደራሊዝም (አፓርታይድ ስርአት) እንዲሁም በመንግስትና ከመንግስት ውጪ ባሉ ፖለቲከኞች በተዘራ ዐማራ ጠል ትርክቶች ሳቢያ መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋዎች፣ ጅምላ ማፈናቀሎች፣ ማሳደዶች እንዲሁም ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሰለባዎች እንደነበረ፤
በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በብዛት ተበትኖ የሚገኘው የዐማራ ህዝብ ተወልዶ ባደገባቸው ቦታዎች ሳይቀር እንደ መጤ ተቆጥሮ የተለያዩ መብቶቹ (የፖለቲካ ተሳትፎ የማድረግ መብቱን ጨምሮ) በማንነቱ ብቻ ሲነፈጉ መቆየታቸውን፤
ከእ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ በጠ/ሚር አብይ አህመድ የሚመራው ኦሮሞ መር ቡድን የስልጣን መንበሩን መቆጣጠሩን ተከትሎ በዐማራው ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ክልሎች የሚደርሰው ጭፍጨፋ ከመቼውም ጊዜ በመጠንም ሆነ በጭካኔ ደረጃ የጨመረ መሆኑን፤
በዋነኛነት በኦሮሚያ ክልል ንጹሀን የዐማራ ብሄር ተወላጆች ማለትም ህጻናት፣ ነፍሰጡሮች፣ አካልጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ህሙማኖች በማንነታቸው ብቻ እለት በእለት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ ሸኔ) ታጣቂዎችና በተባባሪዎቻቸው እንዲሁም በመንግስት የጸጥታ አካላት (የኦሮሞ ልዩ ሀይል አባላትን ጨምሮ) ጭካኔ በተሞላበት መልኩ እየተጨፈጨፉ እንደሆነ፤
በኦሮሚያ ክልል የሚደርሱ ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎችን በሚያጋልጡና በሚያወግዙ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞችና ማህበራዊ አንቂዎች ላይ እዲሁም ተቃውሞአቸውን በ ሰልፍና በሌሎች ሰላማዊ መንገዶች ለመግለጽ በሚሞክሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ የመንግስት ሀይሎች አፈና፣ እስር፣ ግድያና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እየፈጸሙ እንደሚገኝ፤
ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች በሚፈጸሙበት ጊዜና ከተፈጸሙ በኋላ መረጃዎች እንዳይወጡ ለማድረግ በመንግስት በኩል የግንኙነት አገልግሎቶች (የስልክና የበይነ መረብ አገልግሎቶች) እንዲቋረጡ መደረጋቸውን፤
እነኝህና ሌሎች ኢ-ሰብአዊ የሆኑ ድርጊቶች ሲፈጸሙ መንግስት በድርጊቶቹም ሆነ ባሳየው ዳተኝነት ሳቢያ በአፍሪካ የሰዎችና ህዝቦች ቻርተር እውቅና የተሰጣቸውን መብቶችና ነጻነቶች ከማክበርና ከማስከበር አንጻር የተጣለበትን ግዴታ ሳይወጣ በመቅረቱ ተጠያቂነት እንዳለበት በቀረበው አቤቱታ ላይ ተመልክቷል፡፡
Read the joint AAA CHR Statement in English here.
Comments