top of page

በአዲስ አበባ ከተማ እና በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ ያለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ግድያ እና እስራት

Writer's picture: AAA-adminAAA-admin


በአዲስ አበባ ከተማ እና በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ ያለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ግድያ እና እስራት


በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች እና በአዲስ አበባ ከተማና አካባቢው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን (ኢ.ኦ.ተ.ቤ) ተከታዮች ዘንድ የሚከበሩትን ሐይማኖታዊ በዓሎችን ተከትሎ በሠላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃትና እንግልት የአማራ ማኅበር በአሜሪካን እጅግ አሳስቦታል።


የአማራ ማኅበር በአሜሪካ በደረሰው መረጃ መሠረት በአብይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ ታጣቂ ኃይሎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ዕምነት ተከታዮች ዘንድ የተከበረውን የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ ከህግ አግባብ ውጭ ግድያ፣ የአካል ጥቃት፣ የዘፈቀደ እስራት፣ አስገድዶ መሰወር እና የንብረት ውድመት አድርሰዋል። ይህ የመብት ረገጣ በፌዴራሉ ርዕሰ መዲና በአዲስ አበባ ከተማ እና በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች በባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ወልድያ፣ ደብረ-ማርቆስ፣ ቡሬ እና ደምበጫ እና ሌሎችም ከተሞች እንደተፈፀመ ተመዝቧል። በተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶች ዘፈኖችን ዘፍናችኋል እና ታዋቂ የፋኖ መሪዎችን አወድሳችኋል በሚል ክስ በጅምላ እየታሰሩ ወደ ሩቅ (ያልታወቁ) እስር ቤቶች ተግዘዋል።


ከተፈፀሙት ዘግናኝ ጥቃቶች መሐከል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አለፋ ወረዳ በአምጪ ውኃ ቀበሌ (በደልጊ ከተማ አቅራቢያ) ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም. የኦሮሞ ብልጽግና ታጣቂዎች ከ36 ያላነሱ ንፁሀን ዜጎችን በከባድ መሳሪያ በአሰቃቂ ሁኔታ የጨፈጨፉበት ክስተት አንዱ ነው። የአማራ ማሕበር በአሜሪካ ኃይማኖታዊ በዓልን በሚያከብሩ ሠላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀሙትን ዘግናኝ ጥቃቶች እና በደሎች አጥብቆ ያወግዛል። ሆኖም እነዚህ ግፎች የኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ ያለ ምንም ተጠያቂነት ከሚፈፅማቸው ሰፋ ያሉ ዘግናኝ ድርጊቶች የቅርብ ጊዜውቹ ናቸው። ይህንን የበለጠ ለማወቅ እንዲረዳ ከኀምሌ 28/2015 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ 5,052 ንፁሀን ሰዎች በኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ ኃይሎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ 3,935 ሞተው 1,117 እንደቆሰሉ ማኅበሩ መዝግቧል። እነዚህ አኃዞች ከአጠቃላይ ተጎጂዎች መጠን አንፃር አነስተኛውን ቁጥር የሚያሳዩ ናቸው።


ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ በኢ.ኦ.ተ.ቤ. ተከታዮች ላይ ያነጣጠረ በደል እና እንግልት እየፈፀመ ሲሆን በ2015 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን ላይ ሁለንትናዊ ጥቃት ፈፅሟል። ይህ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ለዓመታት ከሚፈፀመው እልቂት በተጨማሪ ነው። በትግራይ ክልል ኃይሎች ሥር የሚገኙት እንደ ራያ አላማጣ፣ የኮረም እና የጠለምት ነዋሪዎችም በትግራይ ክልል እና በፌደራል ኃይሎች ከፍተኛ የጭካኔ እና አፋኝ እርምጃ እየተወሰደባቸው በመሆኑ በነጻነት ማምለክ አልቻሉም።


በኢትዮጵያ በኦሮሞ ብልጽግና አገዛዝ የሚፈፀሙ በተለይም በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግፎችና እና ስደቶች እንዲሁም የዕምነት ነፃነትን የማፈን ተግባሮች የአማራ ማኅበር በአሜሪካን ያሳስቡታል። ይህ አካሄድ መፍትሄ ካልተበጀለት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን ሰላም፣ ነፃነትና መረጋጋት ማደናቀፉን ይቀጥላል።


መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ እና ዘላቂ ሠላም፣ ፍትህ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በማንነታቸው እና/ወይም በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ብቻ በግፍ የታሰሩ ሰዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ ያለው ጦርነት እንዲቆም የአማራ ማኅበር በአሜሪካ አሁንም ጥሪውን ያቀርባል። እንዲሁም የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ አገዛዝ በአማራ ሕዝብ ላይ እየፈፀመ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአገዛዙ ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ማኅበሩ ጥሪውን ያቀርባል።





 

コメント


bottom of page