top of page
Writer's pictureAAA-admin

ከአማራ ማህበር በአሜሪካ የተሰጠ መግለጫ



የአማራ ማህበር በአሜሪካ የአብይ አገዛዝ በ«ኦሮሚያ ክልል» ከዘር ማጥፋት የተረፉትን የአማራ ተፈናቃዮች ሕይወት አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ በግዳጅ ለመመለስ የሚደረግው ሙከራ በፅኑ ያወግዛል!


የአማራ ማህበር በአሜሪካ የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊዎች በ በ«ኦሮሚያ ክልል» ከደረሰባቸው የዘር ማጠፋት ተርፈው በተለያዩ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙትን የአማራ ተፈናቃዮች ያለምንም የጥበቃ እና ራስን የማስተዳደር ማረጋገጫ በግዳጅ ወደ ወለጋ «ኦሮሚያ ክልል» ክልል ለመመልስ የሚደረገት እንቅሰቃሴ እጅግ አሳስቦታል። ይህ ፖሊሲ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቻርተር እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የተደነገጉትን የተፈናቃዮቹን የሰብዓዊ መብቶች የሚጥስ ወንጀል ነው። ተፈናቃዮቹ ቀድሞ በነበሩበት አካባቢ ሲኖሩ ችግር ላይ የጣላችውን እና ሊፈናቀሉ የቻሉበትን ምክንያት፤ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭትን እና አለመርጋጋትን እየፈጠረ ያለው መዋቅራዊ ችግር ሳይፈታ ሰዎቹን ወደ «ኦሮሚያ ክልል» መመለስ ተፈናቃዮቹን አደጋ ላይ ከመጣል የዘለለ የሚያመጣው መፍትሄ አይኖርም። የአማራ ማህበር በአሜሪካ ይህ የጭካኔ ፖሊሲ በአስቸኳይ እንዲቆም እና ለተፈናቃዮቹ፣ በ «ኦሮሚያ ክልል» ለሚገኙ ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦችና በአማራ ክልል እየተደረገ ባለው ጦርነት ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰባቸው ለሚገኙ ንፁሃን ዘላቂ የመፍትሄ እንዲፈለግ ያሳስባል።


ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ እና የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ አገዛዝ ወደ ሥልጣን ከወጡ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል እና አካባቢዎቹ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ታጣቂዎች በአማራ ብሄር እና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያን እምነት ተከታይ ንፁሃን ላይ የዘር ማጥፋት እና የዘር ማፅዳት ወንጀሎች ተፈጽመዋል። በትንሹ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አማራዎች ከምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የዘር ማፅዳት ደርሶባቸዋል። የዚህ የዘር ማጥፋት ተልዕኮ ዋነኛ ተዋናዮች የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የ«ኦሮሚያ ክልል» ልዩ ኃይል፣ ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት)፣ የጉምዝ ታጣቂዎች እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይገኙበታል። በመንግስታዊ ድጋፍ በ«ኦሮሚያ ክልል» ከሚደረገው የዘር ማጥፋት ወንጀል የተረፉት ተፈናቃዮች በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ጊዜያዊ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ። ጉዳዩ ላይ በተደረጉ ምርመራዎች መሠረት አብዛኛው ጊዜያት የዚህ ጥቃት ፈፃሚዎች ተጠቂዎቹ አማራዎች ወደ አካባቢው እንዳይመለሱ መኖሪያ ቤቶቻቸውን እና ንብረቶቻቸውን የሚችሉትን ዘርፈው የቀረውን ያጠፉታል።


የተለያዩ ዓለም አቀፍ የዜና ማሰራጫዎች እንደዘገቡት እና የአማራ ማህበር በአሜሪካ ምንጮች እንዳረጋገጡት በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በሚገኙ የስደተኛ ጣቢያዎች የሚኖሩ ተፈናቃዮች በግዳጅ ወደ «ኦሮሚያ ክልል» እንደሚወሰዱና ፍቃደኛ ሆነው ላልተገኙት ማንኛውም ሰብዓዊ እርዳታ እንደማይሰጥ ተነግሯቸዋል። ይህ ፖሊሲ በኦሮሞ ብልፅግና እና በአማራ ብልፅግና ፓርቲዎች መሃከል በተደረገ ስምምነት መሠረት እንደሚካሄድ ተገልፆዋል። የጀርመን ድምፅ የአማርኛ ዝግጅት እንደዘገበው «[በሰሜን ወሎ በሚገኘው በጃራ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ] ተፈናቃዮች በሦስት ቀን ውስጥ ወደ ደብረ ብርሃን እንደሚወሰዱና ከዛም ወደ ኦሮሚያ ክልል እንደሚሄዱ እንደተነገራቸው ለጀርመን ድምፅ ገልፀዋል»። ኃላፊዎቹ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እንደማይቻልና አንፃራዊ ሠላም ወዳለባቸው የ«ኦሮሚያ ክልል» አካባቢዎች እንደሚዛወሩ ገልፀውላቸዋል። እንደ መረጃዎቹ በተለያዩ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደእነዚህ ቦታዎች ለመመለስ መተማመኛ የሚሆን የሰላም መሻሻል አለመኖሩን ገልፀዋል። በተፈናቃዮቹ ከተነሱት ነገሮች ውስጥ ለተፈፀሙት ወንጀሎች የተጠያቂነት እና የፍትህ ጉዳይ እና በዘር ማጥፋቱ ወንጀል ለጠፋው ሕይወትና ንብረት ካሳ የሚሉት ይገኙበታል።


የአማራ ማህበር በአሜሪካ የዓለም አቀፉ ማህበረተሰብ፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እና የእርዳታ ድርጅቶች ሥልጣን ላይ ባለው የብልፅግና ፓርቲ አገዛዝ ላይ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ግፊት እንዲያደርጉይጠይቃል:

  • ከሥልጣን መልቀቅ - በመላው ኢትዮጵያ በስፋት በተፈፀሙ እልቂቶች ላይ በቀጥታም ይሁን በቸልተኝነት ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት የተሳተፉ ባለሥልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አሊ፣ የ«ኦሮሚያ ክልል» ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ጄኔራል ጌታቸው ጉዲናን ጨምሮ ከሥልጣን እንዲወርዱ እና በሃገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ የአብይ አስተዳደር ፈርሶ የጊዜያዊ የሽግግር መንግሰት እንዲመሠረት ።

  • በግዳጅ እየተፈፀመ ያለውን የአማራ ተፈናቃዮችን ወደ ኦሮሚያና ሌሎች አካባቢዎች የመመለስ ፖሊሲ ባስቸኳይ እንዲያቆሙ።

  • ከመንግስት ውጪ በሆኑ አካላት በኩል የሚከፋፈል አስቸኳይ የሆነ የሰብዓዊ እርዳታ ለተፈናቃዮች እንዲቀርብ።

  • በመላው አማራ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እርዳታ ለማቅረብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አማራ ያልሆኑ ኃይሎች ከአማራ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡ።

  • የአማራ ማህበር በአሜሪካ እነዚሁ አካላት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ የሚከተሉትን ለማስፈፅም ግፊት እንዲያደርጉ ይጠይቃል:

  • በአማራው ላይ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያጣራና ለሰለባዎቹ ፍትህን የሚያሰፍን፤ የኦነግ፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል፣ ሕወሃት እና የጉሙዝ ታጣቂዎች ለፈፀሟቸው ወንጀሎች መሪዎቹን ተጠያቂ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ አካላት የሚሳተፉበት ነፃ የሆነ የተጠያቂነት ሂደትና ሥርዓት እንዲቋቋም። ይህ የተጠያቂነት ሂደት ከዘር ማጥፋቱ ወንጀል ተርፈው የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው እና የቤት፣ የእንስሳት፣ እህል እና የተለያዩ ንብረቶች ጉዳት ለደረሰባቸው የጥቃት ሰለባዎች የሚሰጥ ካሳን የሚያካትት እንዲሆን።

  • ከብሄር እና ከሐይማኖት ልዩነቶች ባሻገር ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች በሠላም፣ በእኩልነት፣ በዲሞክራሲ እና በብልፅግና እንዲኖሩ የሚያስችል የሕገ መንግስት ማሻሻያ እንዲደረግ። ይህ ሂደት የአማራን ሕዝብ ዘላቂ ሠላም እና ራስን በራስ ማስተዳደር እንዲያረጋግጥ የአማራው ማህበረሰብ ተሳታፊ የሚሆንበት እንዲሆን።






Comments


bottom of page